ተረጂነትን በራስ አቅም መተካት የሉዓላዊነትና የክብር መገለጫ ነው

ወይዘሮ ዘለቃሽ ባህሩ

ወቅታዊ
Abdi Awol
April 20, 2026
28 views
ተረጂነትን በራስ አቅም መተካት የሉዓላዊነትና የክብር መገለጫ ነው
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለዜጎች የሚቀርብ ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈንና የውጭ ዕርዳታ ጥገኝነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።
መንግሥት "ተረጂነትን በራስ አቅም መተካት" የሚለውን ሀገራዊ ጥሪ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የየራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ይህም ዜጎች በችግር ጊዜ እርስ በርስ የሚደጋገፉበትን ባህል ከማሳደጉ ባለፈ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በኢኮኖሚ ነፃነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ትልቅ እንቅስቃሴ ነው።
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮም ይህንን ሀገራዊ ጥሪና የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ፖሊሲን ውጤታማ ለማድረግ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት አባል በመሆን በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።
ቢሮው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የፋይናንስ ዘላቂነትን ለማስፈንና ሰብአዊ ድጋፍን በሀገር ውስጥ አቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ተግባራትን በአመራሩና በሠራተኛው አማካኝነት እያከናወነ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘለቃሽ ባህሩ እንደገለጹት ቢሮው ተረጂነትን ዜሮ ለማድረግ የተቀመጠውን ሀገራዊ አቅጣጫ ለመተግበር የሠራተኛውን ተሳትፎ መሠረት ያደረገ ንቅናቄ እያደረገ ነው።
ኃላፊዋ አክለውም ይሄው የሰብአዊ ድጋፍ ሥራ በዘፈቀደ የሚከናወን ሳይሆን በሀገር ደረጃ በራስ አቅም ሰብአዊ ድጋፍን ለማረጋገጥ ተዘጋጅቶ በጸደቀው ደንብ ቁጥር 191/2017 መሠረት ተቋሙ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት አባል በመሆኑ የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በዚሁ ሕጋዊ ማዕቀፍና በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት በቢሮው የሚገኙ 240 የሚጠጉ ሠራተኞችና 7 የሥራ አመራሮች ለወገኔ ደራሽ እኔው ነኝ በሚል መንፈስ ከተጣራ ደመወዛቸው ላይ 0.5 በመቶ በፈቃደኝነት እንዲቆረጥ በማድረግ በየወሩ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህ የሠራተኞች ቁርጠኝነት በ2018 በጀት ዓመት ለሥራ ማስኬጃ ከተመደበው በጀት ከተቀነሰው አንድ በመቶ ጋር ተዳምሮ ከጥር አንድ 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ባለው ሂደት በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን 489 ሺ 722 ብር በላይ ለሰብአዊ ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል።
ይህም ቢሮው "እኔ ለወገኔ ምን አደረግኩ?" የሚለውን የዜግነት ግዴታ ከሕጋዊ ኃላፊነት ጋር በማቀናጀት የተወጣበት ተግባር መሆኑን ኃላፊዋ አብራርተዋል።
እንደ ወይዘሮ ዘለቃሽ ገለጻ ይህ ንቅናቄ ከገንዘብ ድጋፉ ባለፈ ትልቅ የሞራልና የክብር ትርጉም አለው። "ልመናና ተረጂነት ክብርን የሚያሳጣና ነው" ያሉት ኃላፊዋ በተለይም ምግብን መለመን ትልቅ ውርደት መሆኑንና ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋና ወጣት የሰው ኃይል ተጠቅማ ይህንን ታሪክ መቀየር እንዳለባት አሳስበዋል።
ሠራተኛውና አመራሩ ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ተረድቶ ካለው ውስን ገቢ ላይ በደስታና በፈቃደኝነት ድጋፍ ማድረጉ ለሥራው ስኬታማነትና ለተረጂነት አስተሳሰብ መክሰም ትልቅ መሠረት ሆኗል።
ቢሮው በቀጣይም ተቋማዊ ተልዕኮውን ከማሳካት ባሻገር መሰል ማህበራዊና ሰብአዊ ኃላፊነቶችን የመወጣት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በተቋሙ የተጀመረው ይህ የተቀናጀ የድጋፍ አሰባሰብ ሂደት፣ ሌሎች ተቋማትም የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉና ተረጂነትን በራስ አቅም ለመተካት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል።
ባጠቃላይ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ አመራሮችና ሠራተኞች ያሳዩት ቁርጠኝነት ተረጂነትን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚደረገው ጉዞ በጠንካራ መሠረት ላይ መሆኑን ያሳያል።
በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተው የደመወዝ መዋጮና የመንግሥት በጀትን ለሰብአዊ ዓላማ የማዋል ልምድ የዜጎችን እርስ በርስ የመረዳዳት እሴት ከማጎልበት ባለፈ ለሀገር ሉዓላዊነት መጠናከር ትልቅ አምድ ነው።
ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮጵያን ከዕርዳታ ጠባቂነት ወደ ራስ መቻል የምታደርገውን ሽግግር እንደሚያፋጥነው ይታመናል።
<<ከፍታን ማፅናት፤ ነገን ማላቅ>>

Share this news

Subscribe to Newsletter

We'll send you notifications when new news is published.

Comments (0)

No comments yet. Be the first to comment!