ከጠባቂነት ወደ ፐብሊክ ኢንተርፕርነርነት
ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፤ በሪፎርሙ የመነጨው | ፐብሊክ ኢንተርፕርነርነት | አሰልጣኞች በትረፍ ሰዓት ስራ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን ዕድል እውን አደረገ።
የውጤት ተኮር ስልጠናና ተቋማት
Abdi Awol
April 20, 2026
51 views
አንጋፋው ኮሌጅ፤ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተቀረጸውን አዲሱን የሪፎርም ስትራቴጂ (DNAs) መሠረት በማድረግ፣ ተቋማዊ ራስ-ገዝነትንና የባለሙያዎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ገለጸ። ኮሌጁ በጀመረው "ፐብሊክ ኢንተርፕርነርነት" (Public Entrepreneurship) አሰልጣኞች ከመደበኛ ስራቸው ውጭ ባላቸው የትርፍ ሰዓት ተሳትፎ በወር እስከ 60 ሺህ ብር የሚደርስ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ይገኛሉ።
የአመራር ራዕይና ተቋማዊ ሽግግር፦
የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ተስፋዬ አድማሱ እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ከመንግሥት ድጎማ ወጥቶ ራሱን በፋይናንስ ለመደገፍና "ራሰ-ገዝ" ለመሆን በወሰደው ስልታዊ አቅጣጫ መሠረት፣ የምርት ማዕከሉን ወደ እውነተኛ የንግድና የፈጠራ ማዕከልነት ቀይሮታል። ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በ10 የተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ፈቃድ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት ዋና ዲኑ፤ ይህ ሽግግር ተቋሙን በገቢ ከማጠናከሩ ባለፈ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 6.5 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ለማስመዝገብ ማስቻሉን አክለዋል።
"የእኛ ግብ ስልጠናን ከምርት ጋር በማቀናጀት (Project-Based Training) አሰልጣኙም ሆነ ሰልጣኙ የገበያውን ጥራት በተግባር እንዲለማመዱ ማድረግ ነው" ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይህ አሰራር ኮሌጁ ለውጭ አማካሪዎችና ዲዛይነሮች ሊያወጣው የነበረውን ከፍተኛ ሀብት እያስቀረ መሆኑን አስረድተዋል።
ተግባራዊ አፈጻጸምና የአሰልጣኞች ተጠቃሚነት፡
የኮሌጁ ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን አየለ በበኩላቸው፤ ጥቅምት 2017 ዓ.ም የተቋቋመው የምርት ማዕከል ኢንተርፕራይዝ ለአሰልጣኞች አዲስ የገቢ ምንጭ መፍጠሩን ገልጸዋል። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ አሰልጣኞች ከመደበኛ የስልጠና ሰዓታቸው ውጭ በማምሸትና በማደር ጭምር በምርት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። "በዚህም 11 የሚሆኑ አሰልጣኞች በኢንተርፕራይዙ በሚሰሩት ስራ እስከ 60 ሺህ ብር የሚደርስ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ነው፤ ይህም ደመወዝ ብቻ ሳይጠባበቁ በሙያቸው እንዲበለጽጉና ወደ ሌላ ቦታ ሳይሄዱ በግቢያቸው ውስጥ ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል" ብለዋል።
ይህ አሰራር አሰልጣኞችን ብቻ ሳይሆን፣ በደረጃ 4 እና 5 ላይ የሚገኙ ሠልጣኞችንም በአሰልጣኞች የቅርብ ክትትል (Guidance) በሥራው ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ተግባራዊ የክህሎት ሽግግር እንዲፈጠር ማድረጉን አቶ ዘሪሁን አብራርተዋል።
የገበያ ተወዳዳሪነትና ጥራት፡
ማዕከሉ በእንጨትና ብረታ ብረት ማኑፋክቸሪንግ፣ በባዮ-ሜዲካል፣ በአውቶሞቲቭና በጋርመንት ዘርፎች ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለገበያ ያቀርባል። "ለተግባረ-ዕድ ጥራት መደራደሪያ አይደለም" ያሉት አቶ ዘሪሁን፤ ምርቶች ወደ ደንበኛ ከመሄዳቸው በፊት በባለሙያዎች ጥብቅ ፍተሻ እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም የተሽከርካሪ እጥበት (ላቪያጆ) እና የጋራዥ አገልግሎቶችን ለመጀመር መሰረተ-ልማቶች እየተገነቡ መሆኑ ተጠቁሟል።
በአጠቃላይ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአመራር ራዕይንና የተግባር አፈጻጸምን በማቀናጀት፣ መንግሥት የነደፈው የ"11 DNAs" ስትራቴጂ በተግባር እንዴት ውጤት እንደሚያመጣ በተጨባጭ እያሳየ ይገኛል
<<ከፍታን ማፅናት፤ ነገን ማላቅ>>
No comments yet. Be the first to comment!